Get Mystery Box with random crypto!

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን 700 ሚሊየን ብር ፈሰስ ከሚያደርግ የመኪና አምራች ድርጅት | YeneTube

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን 700 ሚሊየን ብር ፈሰስ ከሚያደርግ የመኪና አምራች ድርጅት ጋር የስምምነት ውል ተፈራረመ፡፡

ኮርፖሬሽኑ ኤልአውቶ ኢንጂነሪንግ እና ትሬዲንግ ከተሰኘ የመኪና አምራች ድርጅት ጋር በድሬዳዋ ኢንዱስትሪ ፓርክ መኪና በመገጣጠም ለሀገር ውስጥ እና ለውጪ ገበያ ለማቅረብ ዛሬ በኮርፖሬሽኑ ፅ/ቤት የውል ስምምነት ፈፅሟል፡፡የውል ስምምነቱን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሳንዶካን ደበበ እና የኤልአውቶ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ በቀለ አበበ ተፈራርመዋል፡፡

ዛሬ በነበረው የፊርማ ስነ-ስርዓት ላይ የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሳንዶካን ደበበ ካለፈው በጀት አመት ጀምሮ የሀገር ውስጥ ድርጅቶችን ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ለማስገባት ጠንከር ያሉ ስራዎች እንደተሰሩ የገለፁ ሲሆን የዛሬው የውል ስምምነትም የጥረቱ አካል ውጤት ነው ብለዋል፡፡ዋና ስራ አስፈፃሚው አክለውም ድርጅቱ እስካሁን በፓርኮቻችን ላይ እየሰሩ ካሉ ድርጅቶች በይዘቱ ለየት ያለ መሆኑን ገልጸው በታቀደው ግዜ ወደ ስራ እንደሚገባ ተስፋ አደርጋለሁ ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የኢልአውቶ ኢንጂነሪንግ እና ትሬዲንግ ኃ/የተ/ የግል ማህበር ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ በቀለ አበበ በበኩላቸው ድርጅታቸው ባገኘው እድል ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸው የመረጡት የድሬዳዋ ኢንዱስትሪ ፓርክ የተሟላ አገልግሎቶች ስላሉት ለምርት ሂደታቸው ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር ሲሆን ፓርኩ ከጅቡቲ ወደብ ያለው ርቀትም አጭር በመሆኑ ለስራ ቅልጥፍና ትልቅ ፋይዳ አለው ሲሉ ዋና ስራ አስፈፃሚው አቶ በቀለ አበበ ተናግረዋል፡፡

ድርጀቱ በ700 ሚሊዮን ብር የሚያቋቁመው የመኪና መገጣጠሚያ ፋብሪካ በሙሉ አቅሙ ማምረት ሲጀምር ለ400 ዜጎች ጊዜያዊ እና ቋሚ የስራ እድል በመፍጠር በዓመት 9000 መኪኖችን ለሀገር ውስጥ አና ለውጪ ገቢያ እንደሚያቀርብ ተገልጿል፡፡ኤልአውቶ ኢንጂነሪንግ እና ትሬዲንግ 11ሺ ካ.ሜ ስፋት ያለው ሼድ ለመውሰድ የኪራይ ውል ስምምነት ያደረገ ሲሆን 50 በመቶ ምርቶቹን ለውጪ ገበያ (ኬኒያ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ታንዛኒያ፣ ጅቡቲ እና ሶማሌ ላንድ) የሚያቀርብ ሲሆን ከፊሉን 50 በመቶ ምርቶቹን ደግሞ ለሀገር ውስጥ ገበያ የሚያቀርብ ይሆናል፡፡

@YeneTube @FikerAssefa