Get Mystery Box with random crypto!

በትግራይ ክልል የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሂሳብ ያላቸው ደንበኞች ላይ የተጣለው እገዳ መነሳቱ ተነገረ | YeneTube

በትግራይ ክልል የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሂሳብ ያላቸው ደንበኞች ላይ የተጣለው እገዳ መነሳቱ ተነገረ!

በትግራይ ክልል የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የባንክ ሂሳብ ከፍተው ከጦርነቱ በኋላ ሂሳባቸው የታገደባቸው ደንበኞች አሁን እገዳው እንደተንሳላቸውና ሂሳባቸውን ማንቀሳቀስ እንዲችሉ መፈቀዱን ዋዜማ ራዲዮ ሰምቻለሁ ብላለች።

አንድ ዓመት ሊሆነው የተቃረበው ጦርነት መጀመሩን ተከትሎ በትግራይ ክልል ያለው የባንክ አገልግሎት ሲቋረጥ በትግራይ ክልል የተከፈቱ የባንክ ሂሳቦች እንደይንቀሳቀሱ አብረው መታገዳቸው ይታወሳል።ለእገዳው ምክንያት የነበረው ከፀጥታ ስጋት ጋር የተያያዘ የገንዘብ ዝውውርን መግታት ነበር።

አንድ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከፍተኛ የስራ ሀላፊ ለዋዜማ እንደተናገሩት ትግራይ ክልል ሂሳብ የከፈቱ ደንበኞቹ የታገደባቸውን ሂሳብ ለማንቀሳቀስ ከፈለጉ አቅራቢያቸው ባለ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቅርንጫፍ ቀርበው የታገደባቸውን ሂሳብ ማንቀሳቀስ እንዲፈቀድላቸው የሚጠይቅ ማመልከቻ በመጻፍና ከማመልከቻው ጋርም ማንነታቸውን የሚገልጽ መታወቂያን እንዲሁም የሂሳብ ደብተራቸውን በማያያዝ ጥያቄያቸውን ማቅረብ ይችላሉ።ባንኩም አስፈላጊውን ማጣሪያ አድርጎ ደንበኞቹ ሂሳባቸውን እንዲያንቀሳቅሱ ያደርጋል።

ትግራይ ክልል ተከፍተው በጦርነቱ ሳቢያ መንቀሳቀስ ያልቻሉ ሂሳቦችን እንዲንቀሳቀሱ የማድረጉን ስራ ግን ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ውጭ ሁሉም የግል ንግድ ባንኮች ስለመጀመራቸው ዋዜማ ራዲዮ ማረጋገጥ አልቻለችም። ያነጋገርናቸው የአንድ የግል ንግድ ባንክ ፕሬዝዳንት ስለ ጉዳዩ መረጃ እንደሌላቸው ተናግረዋል።

Via Wazema
@YeneTube @FikerAssefa